ከተራ
ከተራ ማለት ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ፣መክበብ/ከብቦ ማደር ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡
“ከተራ” በመባል የሚታወቀው - ዋዜማው” ሠርግው /1981፣8/ እንደገለጹት “ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረ ከበበ ካለው የግዕዝ ግስ የወጣ ነው፡፡ ከተራ ፍቺውም ውኃ መከተር፣ ወይም መገደብ ማለት ነው፡፡” ብለው ሲፈቱ፣ደስታ ተከለ ወልድ /1962፣ 694/ ደግሞ የጥምቀት ዋዜማ፣ ጥር 10 የጠራ ወራጅ ውኃ የሚከተርበት ታቦትና ሰው ወደ ዠማ ወንዝ የሚወርዱበት ጊዜ” ነው በማለት
ይፈቱታል፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም /1948፣ 555/ ከተረ የሚለውን ቃል በቁሙ፣ “ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ፣ ከለከለ፡፡” ማለት ነው ብለው ይፈቱታል፡፡ በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡
በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣ ‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራል፡ ባሕር፡- የውኃ መሰብሰቢያ (ምእላደ ማይ፣ የውኃ መከማቻ (ምቋመ ማይ) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የውኃ አገር›› /መካነ ማይ፣ ዓለመ ማይ ይለዋል።ይህ ዕለት ታላቅ ዕለት ነው የእግዚአብሔር ማደርያ የኾኑ ታቦታት በአንድነት ተገናኝተው የአዳሪያቸውን አንድ መኾን በምሥጢር የሚያሳዩበት ዕለት ነውና።በእርግጥ ከተራ ከበበ፣ያዘ፣አጠረ፣ዙርያውን ያዘ ማለት በውኃው መገደብ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይኾን የእኛንም በመልካምነት ቅጽር መታጠር የሚገልጽ ሊኾን ይገባል።ክርስትና ማለት ከዲያብሎሳዊ ሥራ ራስን ለመከላከል በሕግጋተ እግዚአብሔር ከተራ ውስጥ ገብቶ መከተር ነውና።ውኃ እንደሚከተር ውኃዊ ሀሳብ የሚፈልቅበት ልቦናችን በትሕትና አጥር መከተር አለበት።
❖ከተራ በሕሊና እግር በእምነት ክንፍ ሲጓዙበት የሚገኝበት ሽፍን ምሥጢር የካህናቱንና የሊቃውንቱን እንዲሁም የምእመናን አንድነት የእግዚአብሔር ማደርያ የተባሉትን ታቦታት መክበብ የሚል ምሥጢር በስሎ የሚወጣበት ጥልቅ የምሥጢር ጉድጓድ ነው።ታቦታቱን ብዙ ሲመስሉ አንድ ናቸው፤አንድም ሲኾኑ ብዙ ናቸው።ለዐይነ ላህሞች የቁጥራቸው ብዛት ብቻ ሊታያቸው ይችል ይኾናል፤ዐይነ ንሥሮች ግን አጥርተው ማየት ስለሚችሉ ወደ ምሥጢሩ ጥልቀት በመንፈሰ ሕሊና ቀድደው ገብተው አንድ በመኾናቸው ምሥጢር ይመሰጣሉ።በኹሉም ታቦታት የሚያድረው አንድ እግዚአብሔር ስለኾነ በአንድነት ይገናኛሉ።ታቦታቱ አንድ ኾነው መሔዳቸው የአማናዊቷን ታቦት የቅድስት ድንግልን አንዲት እናትነት ሰማሳየት በቀር ምን ሊኾን ይችላል??በእርግጥም ቅዱስ ዳዊት ባያት ጊዜ በደስታ የዘለለላት ምሥጢራዊቷ ታቦት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።የክርስቶ አካል የኾነ ኹሉ ይህችን ታቦት ከትሮ ሰማያዊ ዜማ ያቀርብላታል።ለዚህም ነው መጽሐፍ ጽዮንን ክበቧት በማለት ጽዮን የተባለችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን መክተር(መክበብ) እንዳለብን የሚነግረን።ታቦትን ከትሮ መሔድ እመቤትችንን ለሰማያዊ ምስጋና መክተር ነውና እንደምን ይደንቅ ይኾን!ከተራ እንኳን ወደ ከተራው የሔደውን ጌታ ከወለደችልን ድንቋ እናት ጋር ሳያኘናኘን አልቀረም።
❖ከተራ ድንቅ ምሥጢርን ይጨምርልናል እርሱም የነደ እሳትን ውኃ መክተር ነው።ጥር ዐሥር ዕለት ውኃን የከተረ እሳት በውኃ ተከትሮ እንደሚታይ የተገለጠበት ዕለት ነው።እሳት(መለኮት) ውኃ(ትስብእትን) የከተረበት(በተዋህዶ የከበበት) ልዩና ድንቅ ዕለት ነው።በመለኮታዊ ጥበቃ ለመከተር መለኮት በጸጋ እንዲያድርብን የሚያደርግ ሥራ ሊታይብን ይገባል።የምእመናን አንዲትነት በከተራ በኩል ተገልጻ ወጣች።ምእመናን ያለመለያየት አንዲት ከተራን ከትረው በአንዲት የምስጋና መሰላል ከምድራዊ አሠራር ተላቀው ከፍ ከፍ የሚሉባት ልዩ ዕለት ናት።ታቦታቱ ወደ አንዲት ማደርያ ሲገቡ ምእመናን የድንኳን ከተራ ከትረው የዳስንም ከተራ ጥለው በምስጋና አብረው የእግዚአብሔር ማኅደር ኾነው ያድራሉ።ከተራን ድንቅ የሚያደርገው ምሥጢር ይህ ነው።እሳት በውስጣችን እንዲከትር እኛ መሳብያ መልካም ምግባራትን ከእውነተኛ እምነት ጋር እንደመያዣ እናቅርብ።ከተራን ማሰብ ማለት ከታሬ ዓለማት ወምድር በከተረው ዓለም መክተሩን ሳይተው መከተሩን ማድነቅና ዕፁብ ዕፁብ ብለን የምናመሰግንበት ነው።ገዳቢው መገደቡን ሳይተው መገደቡ እንደምን ይረቅ!!!
የከተራውን ምሥጢር አምላካችን ያጠጣን
ጥምቀት
Ø ማለት ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት” ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ማለት አንድ ሰው አንድ አምላክ በሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በተጸለየበትና በተባረከ ውሃ ሦስት ጊዜ ጠልቆ ዳግመኛ ከሥላሴ ተወልዶ የቤተ ክርስቲያን አባል የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን የሚሆንበት ቅዱስ ምስጢር ነው (ማቴ 28፡19-20)፡፡
ምስጢረ ጥምቀት ምስጢር መባሉ ካህኑ ለጥምቀት የተመደበውን ጸሎት አድርሰው ለማጥመ ቅ የተዘጋጀውን ውሃ ሲባርኩት ውሃው ተለውጦ በዕለተ ዐርብ በመስቀል ላይ ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ውሃ ስለሚሆንና ለተጠማቂው ሰው በሚፈጸምለት የሚታይ ሥርዐት የማይታይ የልጅነት ጸጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚሰጥ ነው (ዮሐ 3፡5)፡፡
ምስጢረ ጥምቀትን የመሰረተልን ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ሲመሰርትም በማዘዝ ብቻ ሳይሆን በሥራ በማሳየት ጭምር ነው (ማቴ 3፡17፤ ማር 1፡9፤ ሉቃ 3፡21፤ ዮሐ 1፡31)፡፡
ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እከብር አይል ክቡር የባሕርይ አምላክ ሆኖ ሳለ በዮርዳኖስ ወንዝ በአገልጋዩ (በፍጡሩ) በዮሐንስ የተጠመቀበት ምክንያት፦
1) አንድነቱን ሦስትነቱን ለመግለጽ
2) የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ
3) በእርሱ ጥምቀት የእኛን ጥምቀት ለመቀደስ
4)ለጥምቀታችን ኀይልን ለመስጠት
5) ለአብነት ርሱ ተጠምቆ እናንተም ተጠመቁ ብሎ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በ30 ዘመኑ ጥር 11 ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት፤ ማክሰኞ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡
ጌታችን በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅና የዮርዳኖስ ወንዝ ጌታን ስታይ እንደምትሸሽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 113፡3-5 “ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፤ ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፤ አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል?” በማለት ከ1000 ዓመት አስቀድሞ ትንቢት የተናገረ ሲሆን፤ ብዙ ምሳሌም አለው፨
ምስጢሩ ግን ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን ላይ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ መከራ አጸናባቸው፤ ከዚያም ለኔ የባርነት ስም ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር አላቸው፤ እነሱም “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ” (አዳም የዲያብሎስ ወንድ አገልጋይ ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው አሉ፤ ርሱም ይህንን በዕብነ ሩካም አድርጎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ነበርና፤ ጌታም በዮርኖስ ጥልቅ ወንዝ የተጣለውን የሰው ልጆች ሁሉ የዕዳ ደብዳቤ በጥምቀቱ ለማጥፋት ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡
ዮሐንስ ወደ ጌታችን መምጣት ሲገባው ጌታችን ወደ ዮሐንስ የሄደበት ምክንያት ትሕትናን ለማስተማር ሲሆን ሁለተኛው ለአብነት ለምሳሌ ነው፤ ይኸውም ዮሐንስ ሄዶ አጥምቆት ቢሆን ዛሬ ባለሥልጣናቱ ካህናትን ቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥምቁን ይሏቸው ነበርና ሄዳችሁ ቤተ ክርስቲያን ተጠመቁ ለማለት ሄዷል።
ዮሐንስ ግን ወደርሱ በትሕትና የመጣው አምላኩ ክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?” ሲል ጌታችንም “ጽድቅን ልንፈጽም” ይገባናል ብሎ ትንቢተ ነቢያትን ሊፈጽም እንደመጣ ሲነግረው ዮሐንስ እሺ አለ።
ከዚያም ተያይዘው ወደ ዮርዳኖስ ሲወርዱ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት የዮርዳኖስ ወንዝ 40 ክንድ ወደ ኋላዋ ሸሽታለች በዚህም ዳዊት በመዝ 77፡16 ላይ “አቤቱ፥ ውኆች አዩህ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ።
ጌታችንም ተጠምቆ ከውሃው ከወጣ በኋላ አብ በሰማይ ኹኖ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ” (በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይኽ ነው) ብሎ ሲመሰክር፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፤ አካላዊ ቃል ክርስቶስም በጽንፈ ዮርዳኖስ ቁሞ ታየ፡፡
ይኸውም በምስጢረ ሥላሴ ትምህርት እንደምንረዳው ከሰማይ ኾኖ የመሰከረው ክርስቶስ በቃልነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ያሉበት (ሕልው የኾኑበት) አብ ነው፤ ወርዶ በወልድ ራስ የተቀመጠው አብ በልቡናነት ክርስቶስ በቃልነት ሕልው የኾኑበት መንፈስ ቅዱስ ነው፤ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ የታየው አብ በልቡናነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ሕልው የኾኑበት አካላዊ ቃል ክርስቶስ ነው፤ እንዲኽ አድርገው የአካል ሦስትነታቸውን የፈቃድ አንድነታቸውን ለማስረዳት አብ በአየር ኾኖ መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ታየ፤ አካላዊ ቃል ክርስቶስ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ ታየ።
በዚኽም የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በሚገባ ሲታወቅ በተጨማሪም “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይኽ ነው” ብሎ እግዚአብሔር አብ በመመስከሩ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው በኋለኛው ዘመን ከእመቤታችን ያለ አባት በኅቱም ድንግልና የተወለደው እግዚአብሔር ወልድ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ ብቻ መኾኑ በሚገባ ተረጋግጧል፤ ዕለቱም በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋንያ ሲባል በግእዝ አስተርእዮ በዐማርኛም የመታየት የመገለጥ ጊዜ ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን ስለ ነገረ ጥምቀት የሰማችው ከሌላው ዓለም አስቀድማ ጌታችን ባረገ በጥቂት ወራት (በ34 ዓ.ም) ነው (የሐዋ 8፥26-39)፤ ይህም በዐል ከዘጠኙ ዐበይት በዐላት አንደኛው ሲሆን የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስተምሩን ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ስላመራ ይህንን ለማሰብ ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ያመራሉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በዚህ መልኩ መከበር የተጀመረው ከ515-529 ዓ.ም ለ14 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በአጼ ገብረ መስቀል ዘመን ሲሆን በጊዜው ቅዱስ ያሬድ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ ከዝማሬው በመነሣት ታቦታቱ ጥር 11 ጠዋት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ አምርተው አመሻሹ ላይ ይመለሱ ነበር፡፡
ከዚያም ከ1157-1197 ዓ.ም ድረስ ለ40 ዓመት ኢትዮጵያን በመራው በታላቱ ጻድቅ ንጉሥ በላሊበላ ዘመን በአንድ አካባቢ ያሉ አብያተ ክርስትያናት ታቦታቱ ባንድ ላይ እንዲያከብሩ ንጉሥ ላሊበላ ታላቅ መንፈሳዊ ዐዋጅን አሳውጆ በአንድ አካባቢ፣ ወረዳ፣ ያሉ በአንድ ላይ ማክበር ጀመሩ፤ በርሱ ዘመን የነበሩት ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በጎንደር፣ በሸዋ፣ በአንኮበር፣ በመርጡለ ማርያም እየሄዱ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡
በመቀጠልም ከ1245-1268 ዓ.ም ለ23 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በዐጼ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት ታቦታቱ በባሕረ ጥምቀት ሲውሉ ምእመናን በታላቅ ድምቀት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ እንዲውሉ መንፈሳዊ ዐዋጅ አሳወጁ፡፡
በመቀጠል ከ1426-1460 ዓ.ም ለ34 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በታላቁ ንጉሥ በዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥትም ንጉሡ ከሊቃውንት ጋር በመወያየት የበዐሉን ታሪክ ተከትሎ ታቦታቱ ጥር 10 ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት እንዲወርዱና ጥር 11 እንዲመለሱ ተወሰነ።
ታቦተ ጽዮን በሄደችበት ሁሉ በረከትን ትሰጥ እንደነበር የአቢዳራን ቤት በበረከት እንደሞላች፤ የዮርዳኖስን ባህር እንደከፈለች፣ የኢያሪኮን ቅጽር እንዳፈረሰች፣ የፍልስጤማውያን ጣዖት ዳጎንን ቀጥቅጣ እንዳጠፋች ሀገሪቱ ትባረክ ዘንድ ርኲሳን መናፍስት ይርቁ ዘንድ ምድሪቱ በቃል ኪዳኑ ታቦታት ትቀደስ ዘንድ ታቦታቱ በመጡበት መንገድ እንዳይመለሱ ታላቅ ዐዋጅ አሳውጀው በዐዋጁ መሠረት ዛሬ ድረስ በደመቀ መልኩ በዓሉ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ከባሕር ማዶ ሰዎች ውስጥ ቼሩሊ በዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ቁመቱ 14 ወርዱ 8 ክንድ የኾነ ባሕረ ጥምቀት እንደተዘጋጀ ሲጽፍ፤ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዐጼ ልብነ ድንግል በተገኙበት እጅግ ታላቅ ድንኳን በባሕረ ጥምቀቱ ዙሪያ እንዴት ተተክሎ እንደተከበረ ፍራንቺስኮ አልቫሬዝ ሲጽፍ፤ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን ደግሞ ፔድሮ ፔየዝ ዘግቦት ነበር።
አሁን ባለንበት ጊዜም ዳዊት በመዝ 44፡16 ላይ “በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ” በማለት እንደተናገረ ከመቼውም በበለጠ እግዚአብሔር የወጣቱን ልብ በረድኤት ጎብኝቶት ለቃል ኪዳኑ ታቦታት ክብር አካባቢውን እያስዋበ፣ ታቦታቱ የሚሄዱበትን መንገድ እየጠረገ፤ ታላላቅ ምንጣፎችን ታቦታቱ በሚሄዱበት መንገድ እያነጠፈ ለቃል ኪዳኑ ታቦት እንደ ነቢዩ ዳዊት ከፍተኛ ክብር በመስጠት እግዚአብሔርን እያገለገለ ይገኛል (1ኛ ነገሥት 6፡1-23)፡፡
“የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት” (ኢያ 3፡3)
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ
የጥምቀት በዓል ባሕረ ጥምቀት ታሪካዊ አመጣጥ
ለጥምቀት በዓል ባሕረ ጥምቀት ታሪካዊ አመጣጥ መነሻ የሚሆነን በዋነኝነት የክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄድ ሆኖ ቅድመ በዓል ኤጲፋንያ (ከመገለጥ በዓል በፊት) እስራኤላውያን በብሉይ ኪዳን ወንዝ ወርደው፣ ዣንጥላ አስጥለው፣ ዳስ ሠርተው የመልካም ዛፍ ፍሬና የለመለመ ቅርንጫፍ ወስደው እያንዳንዱ አቅሙ የሚፈቅድለትን ስጦታ እየሰጠ በዓለ መጸለትን (የዳስ በዓልን) እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ በመሄድ “አባቶቻችንን ባህር ከፍለህ ደመና ጋርደህ ያሻገርካቸው” አምላክ አንተ ነህ በማለት የተቀደሰ ጉባዔ በማድረግ በዓሉን ያከብሩ ነበር፡፡ ዘሌ 23፡1-49 ዘጸ 23፡14፣ ዘዳ 16፡16
በኢያሱ የምስፍንና ዘመንም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እግሮች በውሃ ዳር ሲጠልቁ (ወደ ውሃው ሲገቡ) ከላይ የሚወርድው ውሃ ቆሞ እስራኤል ዮርዳኖስን በደረቅ እንደተሻገሩና የእግዚአበሔር እጅ ጠንካራ እንደሆነች ወደፊት የሚነሳው ትውልድ እንዲያውቅ ከማድረግ ጋር በወንዙ ላይ የተደረጉትን ተአምራት የሚገልጽ የዘለዓለም መታሰቢያ (ምልክት) እንደነበራቸው በመጽሐፈ ኢያሱ (3፡14-17) ተጽፏል፡፡
የአረማውያን ቤተሰቦች አይሁድ ለመሆንና ሕገ ኦሪትን ለመጠበቅ ፈቃደኞች በሚሆኑበት ጊዜ ወንዶች የሚገረዙ ሲሆን አይሁድ በመንጻት ሥርዓት በውሃ ታጥበው ከርኩሰታቸው እንደሚነጹ ሁሉ መላው የአሕዛብ ቤተሰብም ከአረማዊነት አኗኗራቸው በውሃ እየተጠመቁ የመንጻት ሥርዓት ይፈጽሙ ነበር፡፡ ዘሌ 12፡8
አበ ትዕግስት ኢዮብና ንዕማን በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ተፈውሰዋል፡፡ ይህም ጥምቀት ከደዌ ነፍስ ለሚያድነውና ሀብተ መንፈስቅዱስ ለሚያሰጠው አማናዊ ጥምቀት ምሳሌ ነበረ፡፡ 2ኛነገ 5፡14፣ ትርጓሜ ወንጌል ማቴ 3፡13 ገጽ 98፡፡ በዚህ መልኩ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ይከበር የነበረው በዓልና ይፈጸም የነበረው ሥርዓተ ጥምቀት ከነበረው ታሪካዊ አመጣጡ በተሻለ መልኩ “ተመልሶ ይምረናል፣ ኃጢአታችንን በባሕሩ ላይ ይጥለዋል” በሚለው በነቢዩ ሚክያስ ትንቢት መሠረት ልጅነትን በሚያስገኝ፣ ጸጋን በሚያሰጥ ሁኔታ ተቀድሶ በጌታ ሰው መሆን ፍጾሜን (ቀጣይነትን) አግኝቷል፡፡ ሚክ 7፡19
ጥምቀተ ዮሐንስ
ለብሉይ ኪዳን መጨረሻ፣ ለሐዲስ ኪዳን መዳረሻ የነበረው ሰማዕተ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ “የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” በማለት ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ሕዝቡን ሁሉ እያስተማረ በቢታንያ ቤተ ራቦ በማእዶተ ዮርዳኖስ ለንስሐ በውሃ ያጠምቅ እንደነበር ወንጌላውያን ጽፏል፡፡ ማቴ3፡3-7፣ ማር 1፡8 ሉቃ 3፡6፣ ዮሐ 1፡28
ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጌታን እያጠመቀው
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጌታን እያጠመቀው
“ወአመ በጽሐ ጊዜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት” የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጅን ላከ፣ ከሴትም ተወለደ፡፡ ተብሎ በቅዱስ ጳውሎስ እንደተጻፈው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ወሰን በሌለው ፍቅር ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸው ዘንድ ከሴት ተወለደ፡፡ (ገላ 4፡4፣ ማቴ 1፡21)
የጌታችን በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅ
በእንግዶች ማረፊያ በቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በግልጥ እየተመላለሰ ከቆየ በኃላ በ30 ዓመቱ በዘመነ ሉቃስ ጥር 11 ቀን በዕለተ ሠሉስ በ10ኛው ሰዓተ ሌሊት በዮሐንስ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ሄደ (ማቴ 3፡11፣ ዮሐ 1፡15-34) ዮሐንስ ግን “እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጂ አንተ በእኔ ልትጠመቅ አይገባም” ብሎ በተከላከለ ጊዜ “ጽድቅን ሁሉ እንፈጽም ዘንድ ይገባናል” አለው፡፡
ጌታም ይህን ተናግሮ ሕግን (ትንቢትን) ሊፈጽም የአዳኝነቱን ሥራ ሊሠራ የቤተክርስቲያን ራስና የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ስለሆነ በሠላሳ ዓመቱ በማዕከለ ባሕር ቆሞ በዕደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቀ፡፡
ሲጠመቅም የሥነ ፍጥረት ገዢ ነውና የዮርዳኖስ ወንዝ ወደፊት መፍሰሱን ትቶ ወደኋላ ተመለሰ፣ ከዚህም ጋር በእርሱ አምነው የሚጠመቁት ሁሉ ሙቀት መንፈስ ቅድስ እንደሚያገኙ ለማረጋግጥና መለኮታዊ ኃይሉን ለመግለጥ ማያት እንደፈሉ ቅዱስ ቄርሎስ “ወፈልሁ ማያት” ውሆች ፈሉ በማለት ተናግሯል፡፡ (መዝ 113፡3)
“እስመ ኦሪት በሙሴ ተወህበት ለነ ጸጋሰ ወጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ኮነ” ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበር ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ ብሎ ዓርከ መርዓዊ ቅዱስ ዮሐንስ እንደመሰከረው በጥምቀቱ ማያትን ቀድሶ እንደምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብ (መጠመቅ)ና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ ሊያድነን ሥርዓተ ጥምቀትን ባርኮ ሰጠን (ዮሐ 1፡17 ቲቶ 3፡5)
ይህንን መሠረት በማድረግ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ የነበሩት የቤተክርስቲያን አባቶች ያመኑትን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማጥመቅ ምሥጢረ ጥምቀትን ይፈጽሙ (ያከናውኑ) ነበር፡፡ (ማቴ 28፡19፣ ዮሐ 19፡2-6)
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከእስክድርያው ፖትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ በተሾመው በአባ ሰላማ ከሳቴብርሃን መምህርነት በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት የክርስትና ሃይማኖት በአዋጅ መሰበኩንና በዓላት በአደባባይ መከበራቸውን ተከትሎ በጃንደረባው አማካኝነት ወደሀገራችን የገባው (የመጣው) የክርስትና ሃየማኖት በቀኖና ቤተክርስቲያን እንዲከናወን ሥርዓት ተሠርቷል፡፡ (በዮሐ 8፡26)
የጥምቀት ባሕር በዓል አከባብር በተለያዩ ዘመናት
ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ክርስቶስና ከሐዋርያት እንዲሁም ከመምህራን በተማረችው (ባገኘችው) ትምህርትና ቀኖና መሠረት በራሷ ቋንቋ የምትገልጠውና የምታከብረው ይህ ጥንታዊ የሆነ የጥምቀተ ባሕር በዓል በዓፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት በ530 ዓ.ም. በሀገረ አቀፍ ደረጃ በሜዳና በወንዝ ዳር መከበር ተጀመረ፡፡ ኢትዮጵያው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ለባሕረ ጥምቀቱ በዓል አከባበር አጥንትን ከሚያለመልም ጣዕመ ዜማ ጋር ጥልቅ ምሥጢር ያለው ማኅሌት (መዝሙር) ደርሷል፡፡ ለምሳሌ ያህል
ለርደተ ባሕሩ ጉዞ (ቃለ እግዚአብሔር)
“ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት በፍሰሐ ወበሰላም”
እግዚአብሔር ወልድ ከሰማያት በደስታና በሰላም ወደ መጠመቂያው ስፍራ ወረደ የሚለውን፣
በማዕከለ ባሕር ለሚፈጸመው ስርዓት
“ነአምን በአብ ወነአምን በወልድ ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እማርያም ዘተወልደ አፍቂሮ ኪያነ መጽአ ኀቤነ ዘነቢያት ሰበኩ ለነ በዮርዳኖስ ተጠምቀ ከመ ይፈጽም ኩሎ ሕገ ወአስተርአየ ገሀደ”፡፡
በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን ነቢያት ይወለዳል ብለው የሰበኩልን ከማርያም የተወለደው እኛን በመውደዱ ወደ እኛ መጣ፡፡ ሕግንም ይፈጸም ዘንድ በዮርዳኖስ ተጠመቀ በግልጥ ታየ፡፡
ታቦታቱ በጥምቀት በዓል ሲከብሩ ለታቦት መነሻ ቃለ እግዚአብሔር (ሲነሣ)
ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ ወበእንተ ጥምቀቱ ሃሌሉያ ሃሌሉያ ሃሌ ሉያ ኃዲጎ ተስዓ ወተስዓተ ነገደ ቆመ ማዕከለ ባህር ገብአ ወወጽአ በሰላም
ክርስቶስ በመወለዱና በመጠመቁ ዛሬ ደስታ ሆነ ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖረው ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ የአዳምንና የሔዋንን (የሰውን ልጅ) የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ (ለማጥፋት) በባህር መካከል ቆመ፣ በሰላም ተመለሰ ማቴ 18፣ የሚለውንና በየምዕራፉ የሚባለውን (የሚዘመረውን) ዝማሬ (ወረብ) ለባሕረ ጥምቀቱ በዓል አዘጋጅቶ በእንደዚህ ዓይነት ማኅሌታዊ ሥርዓት ሲከበር ቆይቷል፡፡
ከዚያም በኋላ ክህነትን ከንግሥና ጋር አስተባብሮ የያዘው ጻድቅና ሐናፄ መቅደስ የሆነው ቅዱስ ላሊበላ በ1140 ዓ.ም. በየአካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በተናጥል ሳይሆን በአንድ ላይ ወደ ባህረ ጥምቀቱ ወርደው በማደር በዓለ ጥምቀቱን እንዲያከብሩ አዋጅ በማወጅ የጥምቀተ ባሕሩን ሥርዓት የበለጠ አጠናክሮታል፡፡ ከሕንፃቹም ሥራ ጋር አብሮ ጌታችን የተጠመቀበትን የዮርዳኖስ ወንዝ አብሮ አካቶታል፣ እስከ አሁንም ድረስ ይህ ቦታ ዮርዳኖስ በመባል ይታወቃል፡፡
በ1426 የነበሩት በሃይማኖትና ሥርዓት ቀናዒነታቸው የሚታወቁት ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከሊቃውንቱ ተዘጋጅቶ በቀረበው የበዓል አከባበር ሥርዓት መነሻነት ታቦታት ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባህረ ጥምቀት ወርደው እንዲያድሩና ሀገርን በኪደተ እግር እንዲባርኩ፣ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ ሥርዓት ሠርተዋል፡፡
ዓፄ ናዖድም እንዲሁም በ1486 ዓ.ም. ምእመናን ከየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚወጡትን ታቦታት አጅበው በማውረድ አጅበው እንዲመለሱ ይህንኑ ሥርዓት ሠርተው ዓዋጅ አውጀዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ መምህራንና በእነዚህ ቅዱሳን ነገሥታት ውሳኔ (አዋጅ) መሠረት ሕዝቡ በከተራ ዕለት በየአካባቢው ለባሕረ ጥምቀት በተመረጠው ወንዝ ውሃውን በኅብረት በመከተር (በመገደብ) አካባቢውን አጽድቶ ታቦት የሚያድርበትን ቦታ አዘጋጅቶ ድንኳን ከተከለ በኋላ ታቦታተ ሕጉን በዝማሬ በሆታና በእልልታ አጅቦ እየወጣ የባሕረ ጥምቀቱ በዓል አከባበር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሁን በምናከብረው ሁኔታ በተናጠል ሳይሆን በኅብረት በየዓመቱ ከጥር 10 እስከ 11 እንዲከበር ተደረገ፡፡
የጥምቀት በዓል አከባበር በዘመናችን
ቀደም ሲል በዘመነ ነገሥት እንደነበረው አሁንም በመዲናዋ አዲስ አበባ በብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ መሪነት እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በየዓመቱ ኢትዮጵያዊነታቸውን (ኦርቶዶክሳዊነታቸውን) በሚገልጽ አለባበስ የምስክሩን ታቦት (ኢያሱ 4፡15) ከፊት ከኋላ ሆነው በማጀብ ሃሌ ሃሌ ሉያ “ተጠምቀ ሰማያዊ በዕደ መሬታዊ” ሰማያዊ ክርስቶስ በመሬታዊ ዮሐንስ እጅ ተጠመቀ እያሉ በማሸብሸብ በልዩ ጣዕመ ዜማና በከበሮ እየዘመሩ ወደየ ባሕረ ጥምቀቱ በመውረድ በዓለ ጥምቀቱን የሁሉን ልብ በሚማርክና ደማቅ በሆነ ሥነ በዓል ያከብሩታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነው በዓለ ጥምቀት ከላይ እንደተገለጸው በተለይ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ፣ በጐንደር ፋሲለደስ ባሕረ ጥምቀት፣ በአክሱም ማይሹም ባሕረ ጥምቀት፣ በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ዮሐንስ አምባ ገጠርጌ ባሕረ ጥምቀትና በመላው ኢትየጵያ በዋዜማው የዮርዳኖስ ምሳሌ የሆነ ባሕር ካለበት ዘንድ ሄደው ለማደር ካህናቱና ምእመናኑ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ሲወጡ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱና ጣዕመ ዝማሬው ለኦርቶዶክሳዊያኑ ብቻ ሳይሆን በቤተክርስያናችን ሥርዓተ አምልኮና በበዓል አከባበራችን ተስበው ወደ ሀገራችን ለሚመጡት ታዳሚዎች፣ እንግዶችና ቱሪስቶች ጭምር የደስታን ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡
በየጥምቀት ባሕሩ ዙሪያ ሰፍረው ድምፀ ይባቤውን ከድምፀ ዝማሬው ጋር አንድ በማድረግ ሲያመሰግኑና ሲዘምሩ የሚያድሩት ሊቃውንቱ፣ ሥርዓተ ቅዳሴውን በማከናወን ለተልእኮ ምስጢር (ለሠሪዐ ቁርባን) የሚተጉት ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ምእመናኑና ምእመናቱ በረከት የሚያስገኘውን የባሕረ ጥምቀቱን ሥርዓት በመፈጸም በተዋሕዶ ሃይማኖት አንድነት ያላቸውን የክርስቶስ ማኅበርና ቤተሰብ መሆናቸውን በእንደዚህ ያለሃይማኖታዊ ሥርዓት ይገልጹታል፡፡
ሥርዓተ ቅዳሴው ከተፈጸመ በኋላ ሲነጋ በወንዙ ዳር (በግድቡ) ጸሎተ አኮቴት ደርሶ፣ አራቱ ወንጌላት ተነበው ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፡፡
ታቦተ ሕጉ ከመነሣቱ በፊት “ኃዲጎ ተስዓ ወተስዓተ ነገደ ቆመ ማዕከለ ባሕር ገብዓ ወወጽአ በሰላም” የሚለውን ግሥ (መዝሙር) በየባሕረ ጥምቀቱ ዘምረው ታቦቱን አክብረው (አንሥተው) በሚያደርጉት የምስጋና ጉዞ የበዓሉ ደስታ ምድርን ይሞላታል፡፡
በእኛ ላይ የነበረውን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰ (ቆላ 2፡14) የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ስብከት በማስታወስ ከመጀመሪያ በዓይን ያዩት በኋላም እነርሱ የተኩት የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት አባቶቻችን ብሔር፣ ቋንቋና ባህል ሳይለያያቸው የበዓላቱን ቀኖና አክብረው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው በጥቂቱ በመታመን በብዙ ላይ ተሹመው ወደ ጌታቸው ደስታ ገብተዋል፡፡ ማቴ 25፡21 (ሉቃ 1፡1-4)
ስለሆነም ተዝካረ ጥምቀቱን (የጥምቀቱን መታሰቢያ) በዓል እንደ ጥንታውያኑ አባቶቻችን መሠረቱ ሳይናወጥ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሳይፋለስ ጸንቶ አንዲኖር ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይገባናል፡፡
በአጠቃላይ የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምታከብረው ሃይማኖታዊ በዓል ይሁን እንጂ በሀገሪቱ የሚገኙ ሕዝቦች ከእምነታቸው ጋር ታሪካቸውንና ባህላቸውን በጋራ የሚያንጸባርቁበት በዓል ከመሆንም በተጨማሪ በሺህ የሚቆጠሩ ሀገር ጐብኚዎችን (ቱሪስቶችን) በመሳብ የሀገራችን ዓለም አቀፋዊ እውቅና ጐልቶ እንዲወጣ ቤተክርስቲያኒቱ አሁንም እንደ ጥንቱ በርትታ ልትሠራ ይገባል እንላለን፡፡
ቀድታችሁ ስጡ (ዮሐ 2፡11)
ጌታ በቃና ዘገሊላ ውሃውን ወደ ወይን ሲቀይር
ወሀቤ ጸጋ ዘእምጸጋ ፍጹም የሆነ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ ፍቅሩ የተነሣ ከፍጹም ጸጋው በልግስና በምልዓትና በቸርነት ፍጥረቱን ሁሉ ይመግባል፣ ይንከባከባልም፣ በመሆኑም የአምላክ ሀብት እንደሰው ሀብት ተቆንጥሮ የሚያልቅ አይደለምና ከፍጹም ጸጋው ወይም ሀብቱ ለፍጡራን ይሰጣል ተብሎ በመጽሐፍ ኪዳን እንደተነገረ፡፡
ይሁንና ከጸጋው ምንም ሳይጐድልበት በስሕተት የወደቀው የሰው ልጅ ከማያልቅ ጸጋው በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ በሁለም ነገር የተራቆተ ሆነ፣ በፈጣሪው ቸርነት የሚያገኛት ጥቂት ስጦታም ረድኤት እየራቃት ጎሮሮውን የማትዘጋ ሆነች፣ በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ረኃብንና ጥምን፣ ጭንቀትንና እርዛትን፣ ኃፍረትንና ውርደትን እንዳስተናገደ ይገኛል፡፡
ክብር ለእርሱ ይሁንና የዓለም ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከረኃብና ከጥም፣ ከውርደትና ከኃፍረት ሊታደግ ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም ተወለደ፣ እንደሰውም በየጥቂቱ አድጐ በሠላሳ ዓመቱ በዮርዳኖር ተጠመቀ፣ ወዲያውኑም ዐርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት ጾመ፣ ከጾም በተመለሰ በሦስተኛው ቀን በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ተገኝቶ በወይን ጠጅ እጥረት ያፈሩትን ሠርገኞች ውሀውን ወደ ወይን ለወጠና ቀድታችሁ ስጡ ብሎ በልግስና በመስጠት የሰዎችን ጭንቀት ኃፍረትና ውርደት አስወገደ፣ የመጀመሪያውን ተአምር አሳየ፣ የክብር አምላክ መሆኑን ገለጠ፣ በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ የተፈለገውም ይኸው በቃና ዘገሊላ የተፈጸመውን ድንቅ የአምላክ ሥራ ነው፡፡
በመሠረቱ ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን በመምረጥ የስብከተ ወንጌል ሥራውን አንድ ብሎ የሚጀምርበት ወቅት ነበረ፣ የወንጌልን ትምህርት ለመቅሰምና ዓለምን ለማስተማር የተመረጠው ደቀ መዛሙርቱ ከሁሉ በፊት የመምህራቸውንና የጌታቸውን ማንነት በመጠኑም ቢሆን እንዲያውቁ ማድረግ የእርሱ ፈቃድ ነበረ፣ ይህንን ቅዱስፈቃዱ ለመግለጽ ደግሞ የቃና ዘገሊላ ሠርግን እንደምክንያት ተጠቅሞ ብዙ ምሥጢር ያለውን አምላካዊ ሥራ በዚህ ሠርግ ቤት አሳየ፣ እነርሱንም በቅደም ተከተል እንደሚከተለው እናያለን፡፡
የሠርጉ ታዳሚዎች
በሀገራችንም ሆነ በሌላው ክፍለዓለም ሠርግ ሲፈጸም ዘመድ አዝማድ፣ ጐረቤትን፣ ወዳጅንና የአካባቢ ሰውን ጠርቶ መጋበዝና የደስታ ተካፋይ እንዲሆን ማድረግ የተለመደ ነው፣ ይህ ባህል በእሥራኤልም የተለመደ ነውና ሠርገኛው ጌታችንን፣ እመቤታችንንና ደቀመዛሙርቱን ወደ ሠርጉ ጠራ፣ ሠርገኛው ከቤተሰቡ መካከል ሳይነጣጥል ሁሉንም በምልአት መጥራቱ አስተዋይና ልባም ሰው የሚያሰኘው ነው፣ የቃና መንደር ለናዝሬት ካላት ቅርበት አንጻር ጌታችንና እመቤታችን ለሠርገኛው ዘመዶች ያም ባይሆን የአካባቢው ሰው መሆናቸውን ስለሚታመን እነርሱን መጥራቱ ብዙም ላያስደንቅ ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን ከተለያየና ራቅ ካለ ስፍራ የተሰባሰቡ እንግዶች ሐዋርያትን አብሮ መጥራቱ የሠርገኛው ደግነትና አስተዋይነት ያሳያል፣ ለጌታ በሠርጉ መገኘትና ለታላቅ አምላካዊ ተአምር መገለጥ ምክንያት እንዲሆን የታደለውም ከዚህ ደግነቱ የተነሣ እንደሆነ ይታያል፡፡ ጌታም ሰውን የሚወድ ጋብቻን የፈጠረና የባረከ አምላክ ነውና ጥሪውን በመቀበል ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ከእናቱ ጋር በሠርጉ ቤት ተገኘ፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንንና ሐዋርያትን አስከትሎ በዚህ ሠርግ መገኘቱ ጋብቻ በአምላክ ዘንድ ምን ያህል የተባረከ የተቀደሰና ተቀባይነት ያለው እንደሆነ የሚያመለከት ነው፤ ከዚህም በላይ እግዚአብሔር አምላክ ጋብቻን በጥንተ ፍጥረት ባርኮ ለፍጡራን ሁሉ እንደሰጠ፣ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምንና ሔዋንን የባረከበት የመጀመሪያው በረከተ ጋብቻ እንደሆነ፣ በኦሪት ዘፍጥረት 1፡27-28፣ ዘፍ 2፡18-25 ተጽፎ እናገኘዋለን፣ የጋብቻ በረከት በቃል ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም አምላክ በጥበብ የወንዱን አካል ለሴቷ እንዲመች፣ የሴቷም አካል ለወንዱ እንዲመች አድርጐ መፍጠሩ፣ በሁለቱም ፆታዎች አካል ውስጥ ከሰው አእምሮና ዓቅም በላይ በሆነ ምሥጢር እርስ በርስ የሚፈላለጉበት ረቂቅና ስሜትን በውስጣቸው እንዲኖር አድርጐ መፍጠሩ፣ ብቻ የተፈቀደ ሳይሆን አስገዳጅም ጭምር አድርጐ እንደፈጠረው መገንዘብ አያዳግትም፣ እንዲህማ ባይሆን ኖሮ የፍጡራን በዘር መተካካት ሂደት አይቀጥልም ነበር፣ በተለይም በዘመናችን አስቸጋሪ ይሆን ነበር፡፡
ይህ ብቻም አይደለም እግዚአብሔር አምላክ ፍጡራን ሁሉ በጋብቻ በረከት እንዲበዙ ካለው መለኮታዊ ፈቃድ የተነሣ ወላጆች ልጆቻቸውን በፍጹም ፍቅርና እንክብካቤ ያሳድጉ ዘንድ ልዩ የሆነ የልጅ ፍላጐት ፍቅር በፍጡራን አእምሮ ውስጥ ማሳደሩ ሌላው የጋብቻን ሥነ-ፍጥረታዊ በረከትን የሚያስረዳ ነው፣ ይሁን እንጅ በሥነ-ፍጥረትና በሕገ ኦሪት እንዲህ ባርኮና ቀድሶ የፈጠረውን በሰው ብቻ ሳይሆን ሕይወት ባላቸው ፍጡራን ሁሉ እንዲደረግና እንዲፈጸም በበረከቱ ለፍጡራን የሰጠውን፣ በሰው ዕውቀትና ጉልበት ሊገታ የማይችለውን የጋብቻ ሕይወት ጌታችን ያስተምርበት በነበረው ጊዜ ጋብቻ አያስፈልግም፣ ኃጢአት ነው፣ ርኩሰት ነው፡፡ እያሉ ያስተምሩ የነበሩ የግሪክ ፈላስፋዎችንና ተከታዮቻቸውን ለማሳፈር ጌታችን ወደ ሠርጉ ቤት ገባ፣ ቤቱንም በበረከት ሞላው፣ ሰዎች ሁሉ ሊፈጽሙትና ሊያከብሩት፣ ሊጠብቁትና ሊንከባከቡት የሚገባ ቅዱስና ንጹሕ መሆን ለማስረዳትና በሠርጉ ቤት ተገኝቶ ጋብቻቸውን በበረከት አጀበው፡፡
በዚህ ገጸ-ንባባ የሚታየው ሌላኛው ቀዋሚ ትምህርት በጌታችን፣ በድንግል ማርያም፣ በሐዋርያትና በምእመናን መካከል ያለው የቅርብ ግንኙነት ነው፣ ጌታችን ያስተማረው ትምህርት ብቻ ሳይሆን የሠራውን ሥራ ሁሉ ነገረ ቤተ ክርስቲናያንን ብሎም ነገረ መንግሥተ እግዚአብሔርን በምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡ በመሆንም ጌታችን፣ እመቤታችንና ሐዋርያት በሠርጉ ቤት መገኘታቸው በምሥጢራዊ ትምህርት የጌታ፣ የእመቤታችንና የቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተክርስቲያን ለዘላለሙ የሚጠራ መሆኑን፣ ሠርገኛው ሁሉንም መጥራቱ ምእመናን ጌታችንን በባህርይ አምላክነቱ ማምለክ፣ ማመስገንና ስሙን ጠርቶ መጸለይ፣ እመቤታችንንና ቅዱሳንንም ስማቸውን እየጠሩ መማፀን የሚገባቸው መሆኑን ያስረዳል፡፡
የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በሠርጉ ቤት
የሰው ዓቅም ውሱንና ጐደሎ መሆኑ ምንጊዜም የታወቀ በመሆኑ ለዚህ ሠርግ የተዘጋጀው የወይን ጠጅ እንግዶቹ ገና በግብዣ ላይ እያሉ በሠርጉ መሃል ተሟጦ አለቀ፤ ተጋባዡ ግን የወይኑን ማለቅ ስለማያውቅ አሁንም እየበላና እየጠጣ ደስታውን ለመግለጽ እንደተዘጋጀ ነው፤ እስኪረካም ድረስ ወይኑ ተደጋግሞ እንደሚሰጠው ተማምኖ በዳሱ ውስጥ ዳር እስከዳር ጥቅጥቅ ብሎ ተቀምጦአል፤ ነገር ግን የወይን ጠጅ ተጨልጦ ስላለቀ ወይን ብሎ ነገር በቤቱ አልነበረም፤ ሠርገኛውና ቤተሰቡም በጭንቀት በኃዘን በድንጋጤና በኃፍረት ተውጠው የሚያደርጉትና የሚያናግሩት መላ ቅጡ ጠፍቶአቸው ግራ ተጋብተዋል፤ ያም ሆኖ ይህንን ችግር ገልጠው ለማንም አልተናገሩም፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር እንደገና ሌላ ቀዋሚ ትምህርት የተላለፈው፤ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፣ የእግዚአብሔር ልዩ ባለሟል የሆነች፣ ጐደሎ ያይደለ ሙሉ ጸጋ የተሠጣት፣ ቅድስት ድንግል ማርያም ርኅራኄና አዘኔታ በተሞላበት አነጋገር “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” በማለት ሁሉን ማድረግ የሚችለውን ሰውም አምላክም ፈጣሪዋም ልጇም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ወይኑን አበርክቶ የሠርገኞቹን ጭንቀትና ኃፍረት ያስወግድ ዘንድ የለመነችውና የማለደችው፡፡ ጌታችንም “አንቺ ሴት ሆይ ካንቺ ጋር ምን አለኝ፣ ነገር ግን ጊዜየ አልደረሰም” በማለት ልመናዋን መቀበሉ አረጋገጠ፣ እዚህ ላይ በጥንቃቄ ሊስተዋሉ የሚገባቸው ነገሮች መኖራቸውን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ በተለይም “አንቺ ሴት” የሚለውና “ካንቺ ጋር ምን አለኝ” የሚለውን በማስተዋል መገንዘብ ያስፈልጋል፤ ጌታ አንቺ ሴት ብሎ እናቱን መጥራቱ “የሴቲቱ ዘር ራስህን ይቀጠቅጣል” ዘፍ 3፡15-17 ተብሎ ለአዳም በተገባው ቃል መሠረት የእባቡን (የዲያብሎስን) ራስ የሚቀጠቅጥ ዘር የተባለው እርሱ መሆኑን፣ ሴት የተባለችም እርስዋ መሆኗን ቃል በቃል በማስቀመጥ ለማስረዳት ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስም ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ 4፡4 ተስፋው በጌታና በእመቤታችን የተፈጸመ መሆኑን ለማሳየት “ከሴት ተወለደ” በማለት ይህንኑ ቃል ተጠቅሟል፤ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ 12፡1-17 ሴቲቱ የእባብን ራስ የሚቀጠቅጥ ልጅ እንደወለደች ጽፎአል፤ ሁሉም ስለ እመቤታችን ሲጽፉ ሴት እያሉ መናገራቸው ፆታዊ ስሟ ከመሆንም ባሻገር የተነገረውተስፋ በእርስዋ የተፈጸመ መሆኑን ቃል በቃል ማስረገጥ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈለጋል፡፡
ካንቺ ጋር ምን አለኝ
“ካንቺ ጋር ምን አለኝ” የሚለው ቃል ስንመለከት ምን ማለት እንደሆነ ከቅዱስ መጽሐፍ በተለምዶ አነጋገር ጋር በሚገናዘብ መረዳት ተገቢ ነው፤ ይህ ቃል መቀበልን ወይም አለመቀበልን ያሳያል የሚለውን በደምብ ማየት ያስፈልጋል፤ ማየትም የሚገባ ከቋንቋው ልምድና መንፈስ ከጌታና ከእመቤታችን እውነተኛ ባህርይ፤ ከጌታና ከእመቤታችን ትእዛዝ አሰጣጥና ከውጤቱ አንጻር ነው፡፡ “ካንቺ ጋር ምን አለኝ” “ካንተ ጋር ምን አለኝ” የሚለው አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጽፎ የሚገኝ የተለመደ ቋንቋ ነው፤ ለምሳሌ (በነገ.ቀዳ 17፡18) ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ልጇ የሞተባት ሱናማዊት ሴት ወደ ነብዩ ኤልያስ በፍጥነት ሄዳ ልጇን እንዲያስነሣላት ስትለምን የልመናዋ ቃል “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ካንተ ጋር ምን አለኝ” የሚል ነበር፤ ይህም ማለት አንተንና እኔን የሚያገናኘን ነገር የለም፤ የራስህ ጉዳይ ነው የሚል አሉታዊ የሆነ የአለመቀበል ቃል ሳይሆን፤ እኔን ከአንተ ጋር ያቃቃረና የማያግባባ ነገር ምን አለኝ፣ የለም፣ ስለሆነም የኔ ልጅ የማታስነሣበት ምክንያት ስለሌለ አድንልኝ፣ አስነሣልኝ የሚል አዎንታዊ አነጋገር ነው፡፡ በመሆኑም ነቢዩ ኤልያስ የቀረበለት ልመና አዎታዊ መሆኑን ስለሚያውቅ ልጇን አስነሥቶላታል፤ ይህ ቃለ እንዳለ (በማቴ 8፡29፣ በማር1፡24፣ በሉቃ 4፡34) ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን፣ የቃል አነጋገር የአዎንታዊ መንፈስ ያለው እንጂ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል በአንዱ ስንኳ የአሉታዊ መንፈስ ያለው ሆኖ የተጠየቀውን ጥያቄ ያስቀረበት ጊዜ አይገኝም፡፡
ከዚህ አንጻር ጌታችን “ካንቺ ጋር ምን አለኝ” ማለቱ አይሆንም አላደርገውም በማለት ልመናዋንና አማላጅነቷን አለመቀበሉን የሚያሳይ አይደለም፤ እርሱ ያለው አንቺ ወይኑን አበርክትላቸው ስትይኝ አይሆንም የሚያስብል ምክንያት ካንቺ ጋር ምን አለኝ የሚል አዎንታዊ መልስ ነው የሰጠው፡፡ ከዚህም ጋር የጌታ ባህርይና የመጣበት መሠረታዊ ሐሳብ ስናስተውል ከዚህ ጋር ይስማማል፤ በመሠረቱ ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋና ዓላማ የተጨነቁትን ለመታደግ፤ እመቤታችንም የለመነችው የተጨነቁትን እንዲታደግ ነው፤ በመሆኑም የቀረበው ልመና ከጌታ ዓላማ ጋር የሚሄድ በመሆኑ ይህንን የማይቀበልበት ምክንያት እንደሌለ በግልጽ እንገነዘባለን፤ ጌታችን የሥነ-ምግባር ሕግ የሰጠን የደነገገ አምላክ ከመሆኑም በላይ የተጨነቁትን እንድንረዳ በስፋት ያስተማረ እርሱ መሆኑ እየታወቀ የተጨነቁትን እንዲረዳ ከቅድስት እናቱ ያውም ምንም የኃጢአትና የስሕተት እንከን ከሌለባት እናቱ የቀረበውን ልመና አይቀበልም ማለት ፍጹም የሚያስኬድ አይደለም፤ ይልቁንም በሁለቱም ፍጹም መግባባት መኖሩንና ጌታም ልመናዋን የተቀበለ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ትልቁ ነጥብ ከጌታ ንግግር በኋላ “የሚላችሁን አድርጉ” ማለቷ ልመናዋን የተቀበለ መሆኑን ያረጋግጣል፤ ባይቀበላት ኖሮ እንዲህ አትልም ነበርና፤ እርሱም “ጋኖቹን ውሃ ሙሉ ቀድታችሁም ለአሳዳሪው ስጡ” በማለት ውሃውን ወይን አድርጐ ማበርከቱ ልመናዋንና አማላጅነትዋን ለመቀበሉ ዋናውና ትልቁ ማረጋገጫ ነው፤ ይህም ጌታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልመናና ጸሎት ተቀብሎ የተጨነቁትን የሚታደግ መሆኑን የሚያረጋግጥና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለ እመቤታችን አማላጅነት አስመልክታ ለምታስተምረው ቀዋሚ ትምህርት መረጃ ነው፡፡
ጊዜየ አልደረሰም
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅድስት ድንግል ማርያምን ልመና እና አማላጅነት የማይቀበልበት ምክንያት እንደሌለ ከገለጸ በኋላ አከታትሎ “ነገር ግን ጊዜየ አልደረሰም” በማለት ስለዋናው ፍጹም የማዳን ምሥጢር እዚህ ላይ ሲናገር እናያለን፡፡ የመድኀኒታችን ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለመንፈሳዊው ድኅነት ማስረጃዎች ናቸው፤ ድውያነ ሥጋን ከደዌ ሥጋ መፈወሱ ድውያነ ነፍስን ከደዌ ነፍስ ለመፈወሱ ማስረጃ ነው፤ እንደዚሁም የቃና ዘገሊላን ውሀ ወደ ወይን ለውጦ የሠርገኛውን ዘመድ አዝማድ ማጠጣቱ አማናዊ ደሙን ሰጥቶ ሕዝቡንና አሕዛቡን በልጅነት ማክበሩን የሚያስረዳ ነው፤ በመሆኑም ጌታችን “ነገር ግን ጊዜየ አልደረሰም” ማለቱ ደሜን አፍስሼ ሁሉንም በመንፈሳዊ ልደት የማከብርበትና እውነተኛውን የደሜን መጠጥ የምሰጥበት ዕለተ ስቅለቴ ገና አልደረሰም ማለቱ ነው፤ በዚህም የሰው ልጅ የልጅነት ጥሙ የሚረካው በጊዜያዊ የወይን መጠጥ ሳይሆን በኋላ በመስቀሉ ላይ በሚፈስ በክቡር ደሙ መሆኑን አርቆና አራቆ መናገሩ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ትልቁ ነገር አምላካችን ትንሹን ነገር ሲለምኑት ትልቁንም ጨምሮ የሚገልጽ አምላክ መሆኑን ነው፡፡ ይህም የተለመደ የአምላካችን አሠራር ነው፤ ነቢዩ ዳንኤል ስለ ኢየሩሳሌም መጠገን መገንባትና ስለሕዝበ እሥራኤል ከምርኮ አገር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ለማወቅ ፈልጐ ሱባኤ በገባ ጊዜ ሕዝቡ የሚመለሱበትንና ኢየሩሳሌም የምትጠገንበትን ዘመን ከመግለጽ ጋር ሕዝበ እግዚአብሔር ምእመናን በክርስቶስ መሥዋዕትነት ከሲኦል ምርኮ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚመለሱበትን ምሥጢረ ሥጋዌ ሲገለጽለት እናያለን (ዳን 9፡20-27) ከዚህም በተመሳሳይ ቅድስት ድንግል ማርያም ስለ ሠርጉ ቤት ወይን ማለቅ አስመልክታ ወይኑን እንዲያበረክትላቸው ስትለምነው ወይኑን አበርክቶ ከመስጠቱም በተጨማሪ ነገሩን በማርዘምና ምሥጢሩን በማስፋት የሰው ዘር ሁሉ መዳኛ ስለሆነው ስለ እውነተኛ የደሙ መጠጥ ገለጸላት፤ በዚህ ሁሉ መድኃኒታች ትንሽ ነገርን ሽተን ስንለምነው ብዙውን አትረፍርፎ እንደሚሰጠን እናስተውላለን፡፡
የድንግል ማርያም ትእዛዝና ምሥጢሩ
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እመቤታችን ድንግል ማርያም የተነጋገሩአቸው ንግግሮች ሁሉ በምሥጢር የተሞሉ ናቸው፤ እርስዋ ልመናዋ በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ምንም ዓይነት መመሪያ እንደሚሰጥ በተሰጣት ጸጋ ስላወቀች አሳላፊዎቹን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” በማለት ለመታዘዝ እንዲዘጋጅ ትእዛዝ አስተላለፈች ይህ የቅድስት ድንግል ማርያም ትእዛዝ ሰው ሁሉ በጌታ የተነገረውን ሁሉ ማመንና መቀበል በእርሱም መኖር እንዳለበት የሚያሳይ መንፈስ ቅዱሳዊ መሪ ቃል ነው፡፡ ጌታችንም እመቤታችን እንደተናገረችው “ጋኖቹን እስከ አፋቸው ምሉአቸው” ብሎ አሳላፊዎቹን አዘዘ ጋኖቹ በውሀ ከተሞሉ በኋላ “ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡ” አለ፤ ይህም ምእመናን በውሀ እየተጠመቁ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚሞሉ ከዚያም ለእግዚአብሔር ልጅነት እንደሚበቁ ምሳሌ ሆኖ ያሳያል፡፡
የአሳዳሪው አድናቆት
የአምላክ ስጦታ ምን ጊዜም ጣፋጭ ነው፣ አስደናቂም ነው የጌታችን ሥራ መጨረሻው በረከትና ሕይወት ነው ሰዎችንም ከጭንቀት የሚታደግ ነው የአምላካችን ፈቃድ የአገልጋዮቹና የወዳጆቹን የቅዱሳን ልመናና አማላጅነት ተቀብሎ ድኅነትን ለሰው ልጃች ማደል ነው፤ በቃና ዘገሊላ የተፈጸመው አስደናቂ ተአምርም ይህንን ሁሉ ምሥጢር ገልጾልናል፡፡
በጣዕሙም ሆነ በበረከቱ ልዩና የአምላክ በረከት ውጤት የሆነው የወይን ጠጅ ቀርቶ መናኛው ወይን እንኳ አልቆባቸው በኃፍረትና በጭንቀት ተወጥረው የነበሩ የሠርግ ባለቤቶች የሠርጉ አሳዳሪ ቀምሶ የማያውቅ ልዩ ጣዕም ያለውን የወይን ጠጅ ቀምሶ በአድናቆት ሲገረም ሲያዩ በደስታ ተሞሉ፣ ጭንቀትና ኃፍረት ማጣትና መሸማቀቅ ተወግደው፣ ደስታና ብልጽግና፣ ጣዕም ያለው ሕይወትና በረከት፣ በሠርግ ቤታቸው ሰፈነ የአምላክ ሥራ ተአምር ነው ይሉታል ይኸው ነው!!
ይህ ጣዕም ያለው በረከትና ሕይወት የተገኘው ከአምላክ እንጂ ከማንም አይደለም፣ዛሬም የሕይወት ጣዕም፣ የኑሮ ጣዕም፣ የቅዱስ ጋብቻ ጣዕም፣ የእውነተኛ ሃይማኖት ጣዕም አልቆባቸው ወይም አጥተው በስንኩል ዓለማዊና ሉላዊ አስተሳሰብ ግራ የተጋቡና በጭንቀት ባህር የሰመጡ ብዙ ናቸው፡፡ ዘላቂና ፍጹም ደስታ የሚገኘው በሃይማኖትና በምግባር ከፈጣሪ ጋር ሲኾን ብቻ ነው፤ ይህን ስናደርግ የሠርጉ አሳዳሪ በወይኑ ጣዕም እንደተደነቀ እኛም በአምላክ በረከት ስንጐበኝ ጣፋጩን ሕይወት እያደነቅን እንጐነጨዋለን፡፡
የጌታችን አምላካዊ ክብር
ጌታችን አምላካዊ ክብሩን ከገለጸባቸው አስደናቂ ተአምራት አንዱና የመጀመሪያው ተአምር ይህ እንደሆነና ደቀ መዛሙርቱም እርሱን አምነው ለመከተል ማጠናከሪያ የሆናቸው ይህ ተአምር እንደሆነ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎአል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ፣ ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የሌለ እንደሆነ በዚህ ተረጋግጧል፤ ቀድሞ ሰማይና ምድርን ሲፈጥር ያለ ንግግር በኃልዩ ብቻ እንደፈጠረ ሁሉ በቃና ዘገሊላም ውሀውን ጠጅ ሲያደርግ ውሀውን ሙሉ፤ ቀድታችሁም ስጡ ከማለት በቀር ውሀው ወደ ወይን ይለወጥ ብሎ ሲጸልይ ወይም እጁን አንስቶ ሲባርከና ሲዳስስ አልታየም፡፡ ያደረገው ንግግርና ንክኪ ሳይኖር የአምላክነቱን ሥራ በኃልዮ በመሥራቱ እርሱ ፈጥሮ የሚገዛና ሁሉን የሚችል አምላክ መሆኑን አሳየ፡፡
በመሆኑም ይህ በዓል ካለው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጥልቅ ትምህርት በመነሣት ቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡
“ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
ይትኣኮት ወይሰባእ ስሙ
ለእግዚአብሔር አምላክነ
ወትረ በኩሉ
ጊዜ ወበኩሉ
ሰአት ሀለ
ሉያ ሰብሕዎ
ወወድስዎ በአሐቲ
ቃል ሣራረሃ
ኩሉ ዓለም